1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ ፌድራል መንግሥት እና የህወሓት ሥምምነት ያልመለሳቸው ጥያቄዎች

Eshete Bekele
ዓርብ፣ ጥቅምት 25 2015

የኢትዮጵያ መንግሥትና ህወሓት የተፈራረሙት ሥምምነት ለደም አፋሳሹ ጦርነት መቋጫ ያበጃል ተብሎ ተስፋ ቢጣልበትም ስለ ኤርትራ ወታደሮች ጉዳይ ምንም ሳይል መቅረቱ ጥያቄ አጭሯል። ሁለቱ ወገኖች ከሥምምነት መድረሳቸውን በአዎንታ የተቀበሉ ቃላቸውን እንዲያከብሩ ግፊት እያደረጉ ነው። ነገር ግን የትጥቅ አፈታት ሒደትን ጨምሮ ግልጽ ያልሆኑ ጉዳዮች አሉ

https://p.dw.com/p/4J5ml
አቶ ሬድዋን ሑሴን እና አቶ ጌታቸው ረዳ የኢትዮጵያ መንግሥት እና ህወሓትን በየፊናቸው በመወከል በደቡብ አፍሪካ ሥምምነት ሲፈራረሙ
ምስል Themba Hadebe/AP/picture alliance

በአዲስ አበባ እና በመቐለ ነዋሪዎች ተስፋ የተጣለበት፤ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና የአውሮፓ ኅብረት ጭምር ድጋፍ የተቸረው የግጭት ማቆም ሥምምነት የተፈራረሙት የኢትዮጵያ ፌድራል መንግሥት እና ህወሓት ቃላቸውን እንዲያከብሩ ከቅርብም ከሩቅም ግፊት እየተደረገባቸው ነው። 

በአፍሪካ ኅብረት መሪነት በሶስት የቀድሞ መሪዎች አሸማጋይነት የተፈረመው ሥምምነት ጥቅምት 24 ቀን 2013 በትግራይ ክልል የተቀሰቀሰውን ጦርነት ማብቂያ ያበጅለታል የሚል ተስፋ ተጥሎበታል። የሁለት ዓመት ጦርነት ያስከተለው ዳፋ የትግራይ፣ የአማራ እና የአፋር ክልሎች ነዋሪዎችን ለብርቱ ሰቆቃ ዳርጓል።

የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ-መንበር ሙሳ ፋኪ ማኅማት "ለትግራይ ሰላም እና መረጋጋት ወሳኝ እርምጃ" ያሉት ሥምምነት በዋናነት ሁለቱ ወገኖች "ለኢትዮጵያ ከፍተኛ ጥቅም ባሳዩት አመራር" የተሳካ እንደሆነ ገልጸዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቱሬዝ ሁለቱ ወገኖች ከሥምምነት መድረሳቸውን አድንቀው "የበርካታ ኢትዮጵያውያን ሕይወት እና መተዳደሪያ የጠፋበትን የሁለት ዓመታት ጦርነት ለማቆም የመጀመሪያው እርምጃ" እንደሆነ ገልጸዋል። የሰላም ሥምምነቱ ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በትግራይበአማራ እና በደቡብ ክልሎች በሚገኙ ነዋሪዎች አዎንታዊ ምላሽ አግኝቷል።

የአፍሪካ ኅብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ ግን የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ አቶ ሬድዋን ሑሴን እና ከህወሓት ከፍተኛ ባለሥልጣናት አንዱ የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ ሥምምነቱን ባለፈው ረቡዕ በደቡብ አፍሪካዋ ፕሬቶሪያ ከመፈረማቸው በፊት ማስጠንቀቂያ ነበራቸው። ሥምምነቱን "አዲስ ጎህ" ብለው ያወደሱት ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ "ይኸ ወቅት የሰላም ሒደቱ መጨረሻ ሳይሆን መጀመሪያ ነው" ሲሉ ተናግረዋል።

አቶ ሬድዋን የኢትዮጵያ ፌድራል መንግሥትን፤ አቶ ጌታቸው ህወሓትን ወክለው የተፈረሙት ሰነድ "በቋሚነት ግጭት በማቆም ዘላቂ ሰላም ለማውረድ የተፈረመ ሥምምነት" የሚል ርዕስ አለው። ሰነዱ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ-መንበር ሙሳ ፋኪ ማኅማት፣ የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝደንት ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ፣ የቀድሞው የኬንያ ፕሬዝደንት ኡኹሩ ኬንያታ እና የቀድሞዋ የደቡብ አፍሪካ ምክትል ፕሬዝደንት ፐምዙሌ ምላቦ ኑካ የፈረሙበት ነው።

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ ሬድዋን ሑሴን ከተደጋጋሚ የሐሳብ ልውውጦች፣ ክፍት እና ዝግ በርካታ እንዲሁም አነስተኛ ተሳታፊዎች ያሏቸው ውይይቶች በኋላ ሥምምነት ላይ እንደተደረሰ በዛሬው ዕለት በትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ገልጸዋል። በዚህ ምክንያት ሬድዋን እንዳሉት "በርካታ የሥምምነት ረቂቆች  በሁለቱም ወገኖች እጅ ይገኛሉ።" ከሥምምነቶቹ ረቂቆች "የተወሰኑት" በመሰራጨታቸው "የተሳሳተ ግንዛቤ ሊሰጡ ስለሚችሉ" የኢትዮጵያ መንግሥት እና ህወሓት የተፈራረሙትን የመጨረሻ ሰነድ አጋርተዋል።

በሰነዱ መሰረት የኢትዮጵያ መንግሥት እና ህወሓት በቋሚነት ግጭት ለማቆም እና "በሥልት፣ በሥርዓት፣ በእርጋታ በተቀናጀ መንገድ የትጥቅ ማስፈታት" ሥምምነት ደርሰዋል። ሥምምነቱ በጦርነቱ የጅምላ ግድያን ጨምሮ አስከፊ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ፈጽመዋል ተብለው የሚወነጀሉት የኤርትራ ወታደሮች ጉዳይ ላይ የሚለው ነገር የለም።

ዳዊት ገብረ ሚካኤል የተባሉ የመቐለ ነዋሪ በሥምምነቱ ደስተኛ ቢሆኑም "የኤርትራ [ወታደሮች] ኢትዮጵያ ውስጥ ገብተው፤ ትግራይ ውስጥ ገብተው እያመሱ ሰው እየገደሉ፤ ብዙ ዘግናኝ ግፍ እያደረሱ ነበር። ነገር ግን በሥምምነቱ [የኤርትራ ወታደሮች ጉዳይ] አልተጠቀሰም። ዝርዝሩ እንዴት ነው የሚሆነው? አፈጻጸሙ እንዴት ነው የሚሆነው? የሚለው ጥርጣሬ አለን" ሲሉ ተናግረዋል።

እርግዓት ገብረስላሴ የተባሉ ሌላ የመቐለ ነዋሪ በበኩላቸው ሥምምነቱ የኤርትራ ወታደሮችን ጉዳይ ባለመጥቀሱ "ችግር ያለበት የሚያስመስል ነገር አለ" ቢሉም ከሚመለከታቸው ማብራሪያ ይጠብቃሉ። እስካሁን በዚህ ጉዳይ ላይ ከኢትዮጵያ መንግሥት፣ ከህወሓት ባለሥልጣናትም ሆነ ከኤርትራ በኩል የተሰጠ ማብራሪያ የለም።

በአፍሪካ ቀንድ ጉዳዮች ላይ በሚያተኩረው ሖርን ዓለም አቀፍ ኢንስቲትዩት ተንታኝ የሆኑት ሙስጠፋ ይሱፍ አሊ ለሥምምነቱ ተግባራዊነት መተማመንን መገንባት አስፈላጊ እንደሆነ ተናግረዋል። በኢትዮጵያ መንግሥት እና በህወሓት መካከል ያለው የመተማመን እጦት ከዚህ ቀደም ሁለቱን ወገኖች ወደ ድርድር ለማቅረብ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ላደረገው ጥረት እንቅፋት እንደነበር በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ እና የአውሮፓ ኅብረት ልዩ ልዑካን ተናግረዋል።

ስትራቴጂስ አፍሪካኒስ የተባለው ተቋም ፕሬዝደንት እና የጂኦፖለቲካ አጥኚ ፓትሪክ ፌራስ ሥምምነቱ ተግባራዊ ለማድረግ የሚቸግር እንደሆነ ሥጋት አላቸው። ፓትሪክ ፌራስ "ሁሉም ነገር እንደታሰበበት ይሰማናል ነገር ግን በጥድፊያ የተከናወነ ነው" ሲሉ ለፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ተናግረዋል።

የአውሮፓ ኅብረት የዉጪ ግንኙነት ኃላፊ ጆሴፕ ቦሬል
በዛሬው ዕለት "ሰላም መፍጠር ጦርነትነትን ከመፍጠር የበለጠ እጅግ ከባድ ነው" ሲሉ የተናገሩት የአውሮፓ ኅብረት የዉጪ ግንኙነት ኃላፊ ጆሴፕ ቦሬል የኢትዮጵያ ተፋላሚ ኃይላት ወደ ድርድር እንዲያመሩ ግፊት ሲያደርጉ ከቆዩ መካከል ናቸው። የአውሮፓ ኅብረት በደቡብ አፍሪካው የዘጠኝ ቀናት ድርድር በተሳታፊነት እንኳ ሳይካፈል ቀርቷል። ምስል Jean-Francois Badias/AP/picture alliance

በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ለሁለት ዓመት ሲፋለሙ የቆዩ ኃይላት ወደ ድርድር እንዲያመሩ ግፊት ሲያደርጉ ከነበሩ መካከል አንዱ የሆኑት የአውሮፓ ኅብረት የዉጪ ግንኙነት ኃላፊ ጆሴፕ ቦሬል ተመሳሳይ ሥጋት አላቸው። ቦሬል "አስቀያሚ" ካሉት የሁለት ዓመት ጦርነት በኋላ የግጭት ማቆም ሥምምነት ቢፈረምም ዘላቂ ተኩስ አቁም ግን "እጅግ አስቸጋሪ ይሆናል" ሲሉ ተናግረዋል። በጀርመን በመካሔድ ላይ ከሚገኘው በኢንዱስትሪ የበለጸጉት የቡድን ሰባት አባል አገራት ስብሰባ ላይ ለጋዜጠኞች አስተያየታቸውን የሰጡት የኅብረቱ የውጭ ግንኙነት ኃላፊ የግጭት ማቆም ሥምምነቱ "መልካም ዜና" ብለው ቢጠሩትም ጉምቱው ዲፕሎማት "ቀላል አይሆንም" ካሉት "ዘላቂ የተኩስ አቁም ላይ መድረስ" እንደሚኖርባቸው ጠቁመዋል። "ሰላም መፍጠር ጦርነትን ከመፍጠር የበለጠ እጅግ ከባድ ነው" ሲሉ ጆሴፕ ቦሬል ተናግረዋል።

የሥምምነቱን መፈረም "በትክክለኛው አቅጣጫ የተወሰደ አንድ እርምጃ" ሲሉ የገለጹት በአምነስቲ ኢንተርናሽናል የምሥራቅ እና ደቡባዊ አፍሪካ ክፍል ኃላፊ ሙለያ ምዋናንያንዳ በበኩላቸው "ግጭት ከተቀሰቀሰበት ጊዜ ጀምሮ ለታየው የተጠያቂነት እጦት ተጨማሪ እርምጃ መወሰድ" አለበት የሚል አቋም አላቸው።  የግጭቱ ተሳታፊዎች የጅምላ እና የዘፈቀደ ግድያ፣ በሴቶች እና ልጃገረዶች ላይ ወሲባዊ ጥቃትን ጨምሮ ለመናገር የሚከብዱ በደሎች ፈጽመዋል" ያሉት ኃላፊው "እነዚህ አሰቃቂ ወንጀሎች በቀላሉ ሊታለፉ አይችሉም" ሲሉ የሥምምነቱ ፈራሚዎች የሚጠብቃቸውን ከባድ ሥራ ጠቁመዋል።

"ሥምምነቱ ለጦር ወንጀሎች እና በሰብዓዊነት ላይ ለተፈጸሙ ወንጀሎች ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ ግልጽ ፍኖተ-ካርታ" እንዳላቀረበ በአምነስቲ ኢንተርናሽናል የምሥራቅ እና ደቡባዊ አፍሪካ ቢሮ ዛሬ አርብ ባወጣው መግለጫ ያሰፈሩት ሙለያ ምዋናንያንዳ "በአገሪቱ የተንሰራፋውን የተጠያቂነት እጦት" ሥምምነቱ ቸል እንዳለ ጠቅሰው "ጥሰቶች እንዲደጋገሙ" ሊያደርግ እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።

እሸቴ በቀለ

ሸዋዬ ለገሰ