1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚኢትዮጵያ

የውጭ ምንዛሪ ግብይት በአቅርቦት እና ፍላጎት ሲከወን ምን አይነት ተጽዕኖ ይዞ ይመጣል?

Eshete Bekele
ረቡዕ፣ ጥር 3 2015

በሁለተኛው ሀገር በቀል የኤኮኖሚ ማሻሻያ የውጭ ምንዛሪ ግብይት በአቅርቦት እና ፍላጎት እንዲከወን የሚያደርግ እርምጃ ይጠበቃል። ይኸ በባንኮች የሚከወነውን የውጭ ምንዛሪ ግብይት በተለምዶ "ጥቁር" ከሚባለው የትይዩ ገበያ ተመን የሚያስማማ ነው። እርምጃው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ባየለበት ኤኮኖሚ ለነጋዴዎች እና ሸማቾች ተስፋ እና ሥጋት አርግዟል።

https://p.dw.com/p/4M23m
US- und Euro-Banknoten
ምስል Mykola Tys/picture alliance

የውጭ ምንዛሪ ግብይት በአቅርቦት እና ፍላጎት ሲከወን ምን አይነት ተጽዕኖ ይዞ ይመጣል?

የኢትዮጵያ መንግሥት የውጭ ምንዛሪ ግብይት በአቅርቦት እና ፍላጎት እንዲወሰን ለማድረግ ሲዘጋጅ እንደ አቶ ሚሊዮን ክብረት ያሉ ባለሙያዎች እርምጃው የውጭ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ኹነኛ ሚና ይጫወታል የሚል ተስፋ አድሮባቸዋል። በገንዘብ ጉዳዮች ላይ በ174 አገሮች የማማከር አገልግሎት የሚሰጠው ቢንደር ዳይከር ኦተ (BDO) የኢትዮጵያ ቢሮ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሚሊዮን ባለፈው ሣምንት የውጭ ባለወረቶች እና ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ገበያ እንዲሰማሩ ለመጋበዝ ዱባይ ነበሩ። በዱባይ ባደረጉት ስብሰባ "ከኢትዮጵያ ገበያ ዶላር ገዝተን ወደ እኛ አገር ትርፋችንን መላክ ስለማንችል አንመጣም" የሚል አስተያየት ከባለወረቶቹ መስማታቸውን አቶ ሚሊዮን ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ለዓለም አቀፍ ባለወረቶች እና ኩባንያዎች በርካታ ዕድሎችን እንደምትታቀርብ ቢታመንም፣ ገበያው ግን ብዙ ፈተናዎች አሉት። እንዲህ በቀላሉ መፍትሔ አይገኝለትም ከሚባለው የውጭ ምንዛሪ እጥረት እስከ ሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ያሉ ተግዳሮቶች የውጭ ኢንቨስትመንትን የሚያሸሹ ናቸው። የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ለረዥም ዓመታት ሥራ ላይ የነበረውን የንግድ ሕግ ማሻሻል፤ የባንክ እና የቴሌኮም አገልግሎት ዘርፎችን ለውጭ ኩባንያዎች መፍቀድን ጨምሮ የተለያዩ ለውጦች ተግባራዊ በማድረግ ላይ ይገኛል።

ከመንግሥት ትኩረቶች አንዱ በ"ሀገር በቀል የኢኮኖሚ መሻሻያ" የተካተተው የውጭ ምንዛሪ ግብይትን በፍላጎት እና አቅርቦት እንዲወሰን የሚያደርግ እርምጃ ነው። ይኸ የውጭ ምንዛሪ እጥረትን በዘላቂነት ለመፍታት እና በገበያ ፍላጎት የሚመራ ተለዋዋጭ የውጭ ምንዛሪ ግብይት ሥርዓት ለመዘርጋት የተያዘ ዕቅድ የኢትዮጵያ መንግሥት ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ጋር ከሶስት ዓመታት በፊት በተፈራረመው ሥምምነት የተካተተ ነው። ከ2013 እስከ 2022 ባሉት ዓመታት ተግባራዊ የሚደረገው የመንግሥት የአስር ዓመት የልማት ዕቅድ "የተረጋጋ የውጭ ምንዛሪ ተመንን ለማረጋጋጥ እና የሀገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ክምችት ለማሳደግ በገበያ ፍላጎትና አቅርቦት የሚመራ የውጭ ምንዛሪ ተመን እንዲኖር" እንደሚደረግ ያትታል።

ሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ
በባንኮች የሚከወነውን የውጭ ምንዛሪ ግብይት ከትይዩ ገበያው ተመን የሚያስተካክለው እርምጃ ተግባራዊ ሲሆን የውጭ ባለወረቶች ትርፋቸውን ወደ አገራቸው መልሰው እንዲወስዱ መንገድ በማመቻቸት የውጭ ኢንቨስትመንት ሊያበረታታ እንደሚችል አቶ ሚሊዮን ክብረት ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። ምስል AFP/E. Jiregna

በባንኮች የሚከወነውን የውጭ ምንዛሪ ግብይት ከትይዩ ገበያው ተመን የሚያስተካክለው እርምጃ ለሶስት ዓመታት ተግባራዊ በሚደረገው ሁለተኛው የሀገር በቀል የኤኮኖሚ ማሻሻያ ምዕራፍ ሥራ ላይ ይውላል ተብሎ የሚጠበቅ ነው። "ሁሉም ኢንቨስተር የሚያውቀው አንድ ሐቅ አለ። ኢትዮጵያ ውስጥ ትርፍህን ማውጣት አትችልም። ማንም ሰው ደግሞ ኢንቨስት የሚያደርገው ለጽድቅ አይደለም። [ትርፍ] ማውጣት ስለማንችል አንገባም ይላሉ። እንደፈለጉ ማውጣት የሚችሉ ከሆነ ግን በገፍ ይገባሉ" ሲሉ አቶ ሚሊዮን እርምጃው ሊያመጣ የሚችለው እምርታ ይገጹታል።

እርምጃው ማን ጠቅሞ ማንን ይጎዳል?

ብር ከዶላር አኳያ ያለውን የምንዛሪ ተመን በከፍተኛ መጠን የሚያዳክም እርምጃ ገቢራዊ ሲሆን ግን ሁሉም የገበያ ባለድርሻዎች ዕኩል ተጠቃሚ አይሆኑም። የኤኮኖሚ ባለሙያዎች እንደሚሉት ቡና፤ ሰሊጥ፤ ቆዳ እና አበባ የመሳሰሉ ምርቶች ለዓለም ገበያ የሚያቀርቡ ነጋዴዎች በእርምጃው ተጠቃሚ ሲሆኑ በውጪ አገር የተመረቱ ሸቀጦች ወደ ኢትዮጵያ የሚያስገቡ ነጋዴዎች በአንጻሩ ጫና ውስጥ ይገባሉ። ዶላር ከብር አኳያ ያለው የምንዛሪ ተመን ከፍ ሲል በሸቀጦች ላይ የሚከተለው የዋጋ ጭማሪ በሁሉም የአገሪቱ ዜጎች ትከሻ ላይ የሚወድቅ ነው። ይኸ ጠንከር ያለ የዋጋ ንረት የማስከተል አቅም ጭምር አለው። ከአስራ ሁለት ዓመታት ገደማ በፊት የኢትዮጵያ መንግሥት ብር ከዶላር አኳያ የነበረውን የምንዛሪ ተመን በ17 ከመቶ ሲያዳከም በገበያው ወደ 40 በመቶ ገደማ የዋጋ ግሽበት ፈጥሮ ነበር።

አቶ ሚሊዮን ግን በተለምዶ ጥቁር እየተባለ የሚጠራው ትይዩ የውጭ ምንዛሪ ግብይት በኤኮኖሚው ውስጥ ባለው ጉልህ ሚና ሳቢያ እርምጃው ተግባራዊ ሲሆን የብር የመግዛት አቅም ተዳከመ ማለት ይቸግራቸዋል። "የ20 እና 50 ሺሕ ዶላር መኪና በ5 ሺሕ ብር ኤልሲ እየተከፈተ እንደሚመጣ እናውቃለን። በአብዛኛው ፋይናንስ የሚደረገው በጥቁር ገበያ እንደሆነ እናውቃለን። ስለዚህ የአብዛኛው ሰው ኑሮ በአብዛኛው ፋይናንስ የሚያደርገው የጎንዮሹ ገበያ ነው" የሚሉት አቶ ሚሊዮን ከመንግሥት ቁጥጥር ውጪ የሚከወነው የውጭ ምንዛሪ ግብይት እውቅና ባይሰጠውም "ኤኮኖሚው ላይ እጅግ ጉልህ የሆነ አስተዋጽዖ" እንዳለው ይሞግታሉ።

በአዲስ አበባ የሚገኝ ሱፐርማርኬት
የውጭ ምንዛሪ ግብይት በአቅርቦት እና ፍላጎት እንዲከወን የሚያደርገው እርምጃ ተግባራዊ ሲሆን የብር የመግዛትን አቅም በማዳከም በገበያው የሸቀጦች ዋጋ ላይ ጭማሪ ሊያስከትል እንደሚችል ባለሙያዎች ይናገራሉ። ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ በተወሰደ ተመሳሳይ እርምጃ 40 በመቶ ገደማ የዋጋ ንረት ተከስቷል። ምስል Seyoum Getu/DW

"አብዛኛው በሥርዓት መነገድ የሚፈልገው ሰው" የውጭ ምንዛሪ ግብይት በአቅርቦት እና በፍላጎት እንዲከወን ሲደረግ ተጠቃሚ ይሆናል የሚል እምነት ያላቸው አቶ ሚሊዮን "ከባንኮች እና ከመንግሥት ባለሥልጣኖች ጋር ባላቸው ግንኙነት ዶላር የማግኘት የተለየ ዕድል ያላቸው ሰዎች" ተጎጂ ሊሆኑ እንደሚችሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

"አብዛኛው ሰው ነጋዴው የሚያመጣለትን ነው የሚቀበለው። አብዛኛው ነጋዴ ደግሞ አንድ ዕቃ ሲያመጣ በእርግጠኝነት አብዛኛው ፋይናንስ የሚደረገው በትይዩው ገበያ እንደሆነ የአደባባይ ሚስጥር ነው" ሲሉ አስረድተዋል። እርምጃው ተግባራዊ ሲሆን በገበያው ሊፈጠር የሚችለውን ተጽዕኖ "በጣም የተጋነነ ሥጋት" የሚሉት አቶ ሚሊዮን "የብር የመግዛት አቅም ይወድቃል የሚለውም አሁን ካለው የበለጠ አይሆንም" ሲሉ ተናግረዋል።

የውጭ ምንዛሪ ግብይትን በአቅርቦት እና ፍላጎት እንዲከወን የሚያደርገው ውሳኔ የኢትዮጵያን ኤኮኖሚ ተወዳዳሪነት ከማሳደግ ባሻገር ለዓመታት ለዘለቀው የውጭ ምንዛሪ እጥረት መፍትሔ ያበጃል የሚል አመክንዮ ይደመጣል። ከአንድ ወር በታች ለሚሆን ጊዜ የሚበቃ ሸቀጥ ከዓለም ገበያ መሸመት የሚችል የውጭ ምንዛሪ ክምችት ያላት ኢትዮጵያ በጎርጎሮሳዊው 2023 እና 2024 ዳጎስ ያለ የውጭ ዕዳ ክፍያ ይጠብቃታል።

በኢትዮጵያ የተመረተ ቡና
ብር ከዶላር አኳያ ያለውን የምንዛሪ ተመን በከፍተኛ መጠን የሚያዳክም እርምጃ ገቢራዊ ሲሆን ቡና፤ ሰሊጥ፤ ቆዳ እና አበባ የመሳሰሉ ምርቶች ለዓለም ገበያ የሚያቀርቡ ነጋዴዎች በእርምጃው ተጠቃሚ ሲሆኑ በውጪ አገር የተመረቱ ሸቀጦች ወደ ኢትዮጵያ የሚያስገቡ ነጋዴዎች በአንጻሩ ጫና ውስጥ ይገባሉ። ምስል DW/J. Jeffrey

እርምጃው የዓለም ባንክ እና ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ከዚህ ቀደም ተግባራዊ እንዲሆን በተደጋጋሚ የወተወቱት ቢሆንም ኤኮኖሚው ኢትዮጵያ የምትሻውን የውጭ ማንዛሪ መጠን ማግኘት የሚችልበት አቅም ካላበጀ ዘላቂ መፍትሔ መሆኑ አጠራጣሪ ነው። የውጭ ምንዛሪ ግብይቱ በአቅርቦት እና ፍላጎት አማካኝነት መከወን ሲጀምር አንድ ዶላር በ80 ብር መመንዘር ቢጀምር አቶ ሚሊዮን እንደሚሉት "ሌላ ቦታ ይሸሽ የነበረው" የውጭ ምንዛሪ "ወደ ኢትዮጵያ ይመጣና የሸቀጥ ገበያው ይረጋጋል።" ኢትዮጵያ ለዓለም ገበያ የምታቀርበውን ሸቀጥ መጠን ለማሳደግ ዶላር የሚገባውን የገበያ ዋጋ ማግኘት አለበት እያሉ የሚሞግቱት አቶ ሚሊዮን ምርቶች ወደ ውጪ አገራት የሚልኩ ነጋዴዎች የሚበረታቱትም ለዶላር ፍትኃዊ የምንዛሪ ተመን ሲኖር እንደሆነ ገልጸዋል።

"ኢትዮጵያ ውስጥ ኤክፖርቱ በጣም የተዳከመው ምርት ወደ ውጪ የሚልኩ ሰዎች የሚገባቸውን ያክል ገንዘብ ስላላገኙ እና አብዛኛውን መንግሥት ስለሚወስደው ነው" የሚሉት የቢንደር ዳይከር ኦተ (BDO) የኢትዮጵያ ቢሮ ዋና ሥራ አስኪያጅ "ኢትዮጵያ የበለጠ ዶላር እንድታመነጭ ዶላሩ የግድ በገበያ ተመን መመንዘር እና ሸቀጦች ወደ ውጪ የሚልኩ ሰዎች መበረታታት አለባቸው" ሲሉ ተናግረዋል። የኢትዮጵያ መንግሥት ውሳኔውን ተግባራዊ ከማድረጉ በፊት "እንደ ዋጋ ማረጋጊያ ከተለያዩ የልማት አጋሮች በቂ ዶላር ባንክ ውስጥ" በማስቀመጥ የውጭ ምንዛሪ እጥረት አለ የሚለውን ሥጋት መቅረፍ እንደሚችል አቶ ሚሊዮን ጥቆማ ሰጥተዋል።

እሸቴ በቀለ

አዜብ ታደሰ