1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚኢትዮጵያ

የኢትዮጵያ ቦንድ ባለቤቶች እና የገንዘብ ሚኒስቴር ባለሥልጣናት ሐሙስ አንገብጋቢ ውይይት አላቸው

Eshete Bekele
ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 3 2016

ኢትዮጵያ በዓለም ገበያ የተሸጠው ቦንድ ወለድ ከ6.625% ወደ 5.5% ዝቅ እንዲል ትፈልጋለች። በታኅሳስ 2017 የሚጠበቀው አንድ ቢሊዮን ዶላር የሚከፈልበት ጊዜ እንዲሸጋሸግ ትሻለች። የኢትዮጵያ ቦንድ ባለቤቶች እና የገንዘብ ሚኒስቴር ነገ ቀጠሮ አላቸው። ቀጠሮው ኢትዮጵያ 33 ሚሊዮን ዶላር ወለድ እንደማትከፍል ካሳወቀች በኋላ የተያዘ ነው

https://p.dw.com/p/4a82O
የኢትዮጵያ የገንዘብ ሚኒስቴር ዋና መሥሪያ ቤት
የመጀመሪያው ውይይት ቢከሽፍም ታኅሳስ 4 ቀን 2016 ከቦንድ ባለቤቶች ጋር ውይይት እንደሚደረግ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ ለሬውተርስ ተናግረዋል።ምስል Eshete Bekele/DW

የኢትዮጵያ ቦንድ ባለቤቶች እና የገንዘብ ሚኒስቴር ባለሥልጣናት ሐሙስ አንገብጋቢ ውይይት አላቸው

የኢትዮጵያ ቦንድ ባለቤቶች እና የገንዘብ ሚኒስቴር ባለሥልጣናት ነገ ሐሙስ አንገብጋቢ ውይይት አላቸው። የውይይቱ ውጤት የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው ዶክተር አብዱልመናን መሐመድ እንደሚሉት በኢትዮጵያ የአንድ ቢሊዮን ዶላር ቦንድ ዕዳ እና ወለድ አከፋፈል ላይ ብቻ ሳይሆን ሀገሪቱ ከሌሎች አበዳሪዎቿ በሚኖራት ግንኙነት ላይ ጭምር ተጽዕኖ ይኖረዋል።

ይኸ ውይይት ኢትዮጵያ ታኅሳስ 1 ቀን 2016 ለቦንድ ባለቤቶች መክፈል የነበረባትን 33 ሚሊዮን ዶላር ወለድ እንደማትከፍል ካሳወቀች በኋላ የተቀጠረ ነው። በውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት የኢትዮጵያ መንግሥት መክፈል የነበረበትን ወለድ መፈጸም እንዳልቻለ የገንዘብ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

ከጥቂት የቦንድ ባለቤቶች ጋር የተደረገው ውይይት በአከፋፈል ረገድ ከሥምምነት ባለመደረሱ ውጤት እንዳላስገኘ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ ለሬውተርስ ተናግረዋል። የመጀመሪያው ውይይት ቢከሽፍም ታኅሳስ 4 ቀን 2016 ከቦንድ ባለቤቶች ጋር ውይይት እንደሚደረግ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ ለሬውተርስ ተናግረዋል።

የቦንድ ባለቤቶች ኮሚቴ በወገኑ ውይይቱ ያለ ውጤት ካበቃ በኋላ የኢትዮጵያ መንግሥት ይጠበቅበት የነበረውን 33 ሚሊዮን ዶላር ወለድ ሳይከፍል መቅረቱ “አላስፈላጊ እና አሳዛኝ” ብሎታል። ኮሚቴው ለተጨማሪ ውይይት ፈቃደኛ መሆኑንም አስታውቋል። 

የኢትዮጵያ መንግሥት እስካሁን ድረስ የሚጠበቅበትን ወለድ ለቦንድ ባለቤቶች ሲከፍል ቆይቷል። በጎርጎሮሳዊው 2018-19 እንኳ 66.25 ሚሊዮን ዶላር ወይም 1.8 ቢሊዮን ብር ወለድ የኢትዮጵያ መንግሥት እንደከፈለ የሲፊየስ ካፒታል ትንታኔ ያሳያል።

ከኢትዮጵያ ዩሮ ቦንድ ገዢዎች ጋር በሚቀጥለው ሣምንት ውይይት ሊደረግ ነው

የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው ዶክተር አብዱልመናን መሐመድ ከኢትዮጵያ ቦንድ ባለቤቶች መካከል ትልልቅ ባንኮችን ጨምሮ ተቋማዊ ባለወረቶች በዚህ ውይይት ሊሳተፉ እንደሚችሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። አሜሪካን ቢከን ፍሮንቲየር ማርኬትስ ፈንድ፣ ቴምፕልተን ኢመርጂንግ ማርኬትስ ቦንድ ፈንድ፣ ፒክቴት ግሎባል ኢመርጂንግ ዴብት ባለፉት ዓመታት ከኢትዮጵያ ቦንድ ዳጎስ ያለ ድርሻ ያላቸው ተቋማት ነበሩ።

ኢትዮጵያ መክፈል ቢሳናት ጉዳቱ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ብቻ ሳይሆን የአንድ ቢሊዮን ዶላር ቦንድ ባለቤት ለሆኑ አበዳሪዎች ጭምር እንደሆነ የገለጹት ዶክተር አብዱልመናን ሁለቱ ወገኖች ሊስማሙ እንደሚችሉ ይናገራሉ።

ዛምቢያ በዓለም ገበያ የሸጠችውን የ3 ቢሊዮን ዶላር ቦንድ መክፈል በተሳናት ወቅት በተመሳሳይ ሒደት ውስጥ ማለፏን በምሳሌነት የጠቀሱት የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው “ለሁለቱም ጥቅም ስላለው ሐሙስ ይማማሉ የሚል እምነት አለኝ” ሲሉ ተናግረዋል።

ሐሙስ በሚደረገው ውይይት የኢትዮጵያ ቦንድ ባለቤቶች እና የገንዘብ ሚኒስቴር ባለሥልጣናት ከሥምምነት ይደርሳሉ የሚል ተስፋ ዶክተር አብዱልመናን ቢኖራቸውም የወለድ ምጣኔ እና የአከፋፈል ሁኔታን ጨምሮ ልዩነት እንዳላቸው አልዘነጉም።

የኢትዮጵያ መንግሥት በመጪው ዓመት የሚጎመራው የአንድ ቢሊዮን ዶላር ቦንድ የመጨረሻ ክፍያ በአራት ዓመታት ተከፋፍሎ እንዲከናወን ይፈልጋል። የወለድ ምጣኔውም ከ6.625 ወደ 5.5 በመቶ ዝቅ እንዲል ከቦንድ ባለቤቶች ጋር በተደረገው ውይይት ሐሳብ አቅርቧል።

“የኢትዮጵያ መንግሥት የወለድ ምጣኔው ወደ 5.5 በመቶ ይቀነስ ብሏል፤ የአከፋፈል ሁኔታው ከአራት ዓመት ተኩል በኋላ በስምንት ክፍያ ይሁንልኝ ብሏል” የሚሉት ዶክተር አብዱልመናን የቦንድ ባለቤቶች ግን በቀረበው ምክረ-ሐሳብ እንዳልተስማሙ ገልጸዋል። ክፍያው በጎርጎሮሳዊው 2028 እንዲፈጸም የቦንዱ ባለቤቶች ምክረ-ሐሳብ እንዳቀረቡ የገለጹት ዶክተር አብዱልመናን “ወለዱ ላይ አንስማማም” ማለታቸውን ገልጸዋል።

የዕዳ አከፋፈልን በተመለከተ ኢትዮጵያ ማሻሻያ የምትሻው ከቦንድ ባለቤቶች ብቻ አይደለም። ኢትዮጵያ በቡድን 20 የጋራ ማዕቀፍ (G20's Common Framework) በኩል የዕዳ አከፋፈል ማሻሻያ ለማድረግ ውይይት ላይ ትገኛለች። ውይይቱ እስኪጠናቀቅ ድረስ የፓሪስ ክለብ አባላት ለኢትዮጵያ መንግሥት የሁለት ዓመት የዕዳ ክፍያ እፎይታ ሰጥተዋል። ይኸ እፎይታ ለኢትዮጵያ 1.5 ቢሊዮን ዶላር ወጪ እንደሚያድን የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምኅረቱ ተናግረዋል።

አዲስ አበባ ስታዲየም አካባቢ
የኢትዮጵያ መንግሥት የዩሮ ቦንድ ባለቤቶች ብድር “እንደ ሌላው የዕዳ አይነት መፍትሔ” እንዲበጅለት ይፈልጋልምስል DW

ከፓሪስ ክለብ በተጨማሪ ለኢትዮጵያ ጠቀም ያለ ገንዘብ ያበደረችው ቻይና ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት የአንድ ዓመት የዕዳ ክፍያ እፎይታ ሰጥታለች። የገንዘብ ሚኒስቴር ከቻይና አበዳሪ ተቋማት ጋር የዕዳ አከፋፈል ሽግሽግን የተመለከተ ውይይት እንዲያደርግ ተወስኗል።

የኢትዮጵያ መንግሥት የዩሮ ቦንድ ባለቤቶች ብድር “እንደ ሌላው የዕዳ አይነት መፍትሔ” እንዲበጅለት ይፈልጋል። የዩሮ ቦንድ ባለቤቶች ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያን የመክፈያ ጊዜ ከ2024 ወደ 2029 ወይም 2030 የማራዘም ፍላጎት እንዳላቸው ሬውተርስ ዘግቧል።

የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው ዶክተር አብዱልመናን የኢትዮጵያ መንግሥት አካሔድ ሁሉንም አበዳሪዎች በፍትኃዊነት እኩል ከማስተናገድ ፍላጎት የመነጨ ሊሆን እንደሚችል እምነት አላቸው። ኢትዮጵያ የዕዳ አከፋፈል ስትሻ ሁሉንም አበዳሪዎቿን በፍትኃዊነት ማስተናገድ ይጠበቅባታል የሚሉት ዶክተር አብዱልመናን “የቦንድ ባለቤቶችን የተለየ የብቻ ጥቅም የምትሰጥበት አንድም ምክንያት የለም። ምክንያቱም የተለየ ጥቅም የሚሰጣቸው ከሆነ ሌሎች አበዳሪዎች ጥያቄ ያነሳሉ” ሲሉ ተናግረዋል።

”የኢትዮጵያ መንግሥት የተከተለው አካሔድ ማንኛውም ተበዳሪ እና ችግር ውስጥ ያለ ሀገር የሚያደርገው ነው” የሚሉት ባለሙያው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ለቦንዱ ባለቤቶች 33 ሚሊዮን ዶላር ወለድ ሳይከፍል የቀረው በውጭ ምንዛሪ እጥረት ነው የሚለው አመክንዮ አይዋጥላቸውም።

ከቦንዱ ባለቤቶች ጋር የሚያደርገው ውይይት ግን መንግሥት ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት በሚኖረው ግንኙነትም ሆነ በቡድን 20 የጋራ ማዕቀፍ የዕዳ አከፋፈል ሽግሽግ ለማድረግ አስተዋጽዖ እንደሚረው አስረድተዋል።

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ
የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ሥልጣን ላይ ሳሉ የተሸጠው የኢትዮጵያ የአንድ ቢሊዮን ዶላር ቦንድ 6.6 በመቶ ገደማ ወለድ ይከፈልበታልምስል picture-alliance/AP Photo

የኢትዮጵያ መንግሥት ከቦንድ ባለቤቶች ጋር የሚያደርገው ድርድር ከተሳካ “በጣም አዎንታዊ” ሚና እንደሚኖረው የጠቀሱት የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው “የንግድ ብድሩን የኢትዮጵያ መንግሥት በአግባቡ ተደራድሮ የአከፋፈል ሽግሽጉ ላይ ከተስማማ ለሚቀጥለው ድርድር በጣም ይጠቅመዋል” ሲሉ አስረድተዋል። ሳይሳካ ከቀረ ግን ዶክተር አብዱልመናን እንደሚሉት “ድርድሩን በጣም የተራዘመ እንዲሆን ያደርገዋል”

የአንድ ዶላር የኢትዮጵያ ቦንድ ሰሞኑን የሚሸጥበት ዋጋ 64 ሣንቲም ገደማ ደርሷል። ባለፉት ዓመታት የኢትዮጵያ ፖለቲካ በቀውስ ሲናጥ ቦንዱ በዓለም ገበያ የሚሸጥበት ዋጋም አብሮ ሲዋዥቅ ቆይቷል። ይኸ  ቦንድ ለገበያ ሲቀርብ የኢትዮጵያ መንግሥት ለገዢዎች አገሪቱ ሊገጥሟት ይችላሉ ያላቸውን ቀውሶች በዝርዝር አስቀምጧል።

በ108 ገፆች የተቀነበበው ሰነድ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት፣ በቀጣናው የሚቀሰቀስ ፖለቲካዊ አሊያም ወታደራዊ አለመረጋጋት በኢትዮጵያ ኤኮኖሚ ላይ ጫና ሊያሳድሩ ከሚችሉ አደጋዎች መካከል ሊሆኑ እንደሚችሉ አስጠንቅቆ ነበር።  ቦንዱ ከተሸጠ በኋላ በሀገሪቱ የሚካሔዱ ምርጫዎች ፖለቲካዊ አለመረጋጋት አሊያም የፖሊሲ ለውጥ ሊያስከትሉ እንደሚችሉም አስቀድሞ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል።

እሸቴ በቀለ

ሸዋዬ ለገሠ