1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚኢትዮጵያ

የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ትንበያ ስለ ኢትዮጵያ ኤኮኖሚ ምን ይላል?

ረቡዕ፣ ጥቅምት 9 2015

ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) በ2023 የኢትዮጵያ ኤኮኖሚ በ5.3 በመቶ ያድጋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ይፋ አድርጓል። ይኸ የዕድገት መጠን ከስድስት ወራት በፊት አይ.ኤም.ኤፍ ከሰጠው ትንበያ በ0.4 በመቶ ዝቅ ያለ ነው። በትንበያው መሠረት በዓመቱ ኢትዮጵያ የሚኖራት የውጭ ምንዛሪ ክምችት ለ18 ቀናት የሚበቃ ሸቀጥ መሸመት የሚችል ነው።

https://p.dw.com/p/4IQtT
Kristalina Georgieva
ምስል Dursun Aydemir/AA/picture alliance

በጎርጎሮሳዊው 2023 የኢትዮጵያ ምጣኔ ሐብት 5.3 በመቶ ያድጋል ተብሎ እንደሚጠበቅ የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ትንበያ ያሳያል። ይኸ የዕድገት መጠን ከስድስት ወራት በፊት አይ.ኤም.ኤፍ ከሰጠው ትንበያ በ0.4 በመቶ ገደማ ዝቅ ያለ ነው።

ድርጅቱ በሚያዝያ 2014 ይፋ ባደረገው የአገራት የምጣኔ ሐብት ዕድገት ትንበያ መሠረት በ2023 የኢትዮጵያ ኤኮኖሚ 5 ነጥብ 7 በመቶ ያድጋል ተብሎ ይጠበቅ ነበር። ተቋሙ የኢትዮጵያን ኤኮኖሚዊ ዕድገት ትንበያ ለምን እንደከለሰ የተጠየቁት በዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የአፍሪካ ክፍል ኃላፊ አበበ አዕምሮ ሥላሴ በኢትዮጵያ ጉዳይ ማብራሪያ ከመስጠት በመታቀባቸው መልስ አልሰጡም።

የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ቃል አቀባይ በኢ-ሜይል ለዶይቼ ቬለ በሰጡት ምላሽ ትንበያው "በብርቱ ድርቅ እና በዩክሬን በተቀሰቀሰው ጦርነት ዳፋ ምክንያት" እንደተከለሰ ምጥን ያለ መልስ ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ ምጣኔ ሐብት "በመጠኑ ያገግማል" ተብሎ እንደሚጠበቅ የገለጹት ቃል አቀባዩ በ2022/23 የበጀት ዓመት ኤኮኖሚው በአገሪቱ ያለው ግጭት እና የኮቪድ 19 ወረርሽኝ የተራዘመ ተጽዕኖ የተጫኑት እንደሚሆን ገልጸዋል። በዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ትንበያ መሠረት ከሁለት ወራት በኋላ በሚጠናቀቀው የጎርጎሮሳዊው 2022 የኢትዮጵያ ምጣኔ ሐብት በ3.8 በመቶ ያድጋል።

በትንበያው መሠረት ሊጠናቀቅ ሁለት ወራት ገደማ ብቻ በቀሩት የጎርጎሮሳዊው 2022 ከኢትዮጵያ አጠቃላይ የምርት መጠን (GDP) 46.4 በመቶ የነበረው የመንግሥት ዕዳ በሚቀጥለው ዓመት ወደ 40.4 በመቶ ዝቅ ይላል።የኢትዮጵያ የውጭ ብድር መጠን በ2022 ከአገሪቱ አጠቃላይ የምርት መጠን 25.5 በመቶ የነበረ ሲሆን በሚቀጥለው ዓመት ደግሞ ወደ 22.4 በመቶ ዝቅ እንደሚል ትንበያው ያሳያል።  

የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ትንበያ እንደሚያሳየው ኢትዮጵያ በ2023 የሚኖራት ውጭ ምንዛሪ ክምችት ለአንድ ወር እንኳ የማይበቃ ሊሆን ይችላል። በ2023 ኢትዮጵያ የሚኖራት የውጭ ምንዛሪ ክምችት መጠን ለ18 ቀናት ብቻ የሚሆን ሸቀጥ እና አገልግሎት መሸመት የሚችል እንደሚሆን ባለፈው ሣምንት ይፋ ባደረገው ሪፖርት አስቀምጧል። ይኸ የአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ክምችት መጠን ካለፉት አምስት ዓመታት አኳያ ዝቅተኛው ነው።

ከሰሐራ በርሐ በታች የሚገኙ የአፍሪካ አገራት ምጣኔ ሐብት ትንበያ ምን ይመስላል?

የአፍሪካ አገራት በዓመቱ የሚኖራቸው ምጣኔ ሐብታዊ ዕድገት እንደየ ኤኮኖሚያቸው ጠባይ የተለያየ ቢሆንም ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት እንዳለው አመርቂ የሚባል አይደለም። በዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የአፍሪካ ክፍል ኃላፊ አበበ አዕምሮ ሥላሴ ባለፈው ዓርብ ጥቅምት 4 ቀን 2015 በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ "በ2021 የቀጠናው ኤኮኖሚያዊ ዕድገት 4.7 በመቶ የነበረ ሲሆን ከፍተኛ ቅናሽ አሳይቶ በዚህ ዓመት 3.6 በመቶ ይሆናል ብለን እንጠብቃለን። የዓለም አቀፍ የኤኮኖሚ መቀዛቀዝ፣ የዓለም አቀፍ ፋይናንስ ሁኔታዎች መጥበቅ እና ያልተረጋጋ ሸቀጦች ዋጋ ቀድሞም የተራዘመ የወረርሽኝ ዳፋ ያልተላቀቀው ቀጠና ላይ ተጽዕኖ  ያሳድራሉ። የ2023 ዕድገትም በቀጠናው ደብዝዞ ወደ 3.7 በመቶ ገደማ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል" ሲሉ ተናግረዋል።

"አስፈሪ" የምግብ ዋስትና እጦት ያስከተለው ዓለም አቀፍ የዋጋ ንረት

የአፍሪካ አገራት ማዕከላዊ ባንኮች ከቁጥጥራቸው ውጪ በሆነ ምክንያት ተከስቶ አበበ "አስፈሪ" ያሉትን የምግብ ዋስትና እጦት ያስከተለ የዋጋ ንረት ለመቆጣጠር ፈታኝ ሁኔታ ተጋርጦባቸዋል። ባለፈው አርብ ይፋ የሆነው የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የምጣኔ ሐብት ትንበያ ከሰሐራ በርሐ በታች በሚገኙ አገራት 123 ሚሊዮን ሰዎች ወይም ከቀጠናው ነዋሪዎች 12 በመቶው ብርቱ የምግብ ዋስትና እጦት እንደገጠማቸው አትቷል።

የዩክሬን ጦርነት፣ እየተባባሰ የሚሔድ አለመረጋጋት እና በአንዳንድ የአኅጉሩ አካባቢዎች የተከሰተ ድርቅ ዋና ዋና ምክንያቶች ናቸው። በኢትዮጵያ፣ ሶማሊያ እና አንዳንድ የኬንያ አካባቢዎች አምስተኛ ተከታታይ የዝናብ ወቅት ይከሽፋል የሚለው ሥጋት ችግሩን የበለጠ ሊያባብሰው እንደሚችል ይጠበቃል።

በሶማሊያ የተከሰተ ድርቅ ወደ ጠኔ ይከፋል የሚል ሥጋት አይሏል።
በኢትዮጵያ፣ ሶማሊያ እና አንዳንድ የኬንያ አካባቢዎች አምስተኛ ተከታታይ የዝናብ ወቅት ይከሽፋል የሚለው ሥጋት የምግብ ዋስትና እጦትን የበለጠ ሊያባብሰው እንደሚችል ይጠበቃል።ምስል Mariel Müller/DW

አበበ አዕምሮ ሥላሴ "ባለፉት ከአስራ አምስት እስከ አስራ ስምንት ዓመታት ትልቅ ጉዳይ ያልነበረው የዋጋ ንረት አሁን በበርካታ አገራት አሳሳቢ ሆኗል። በጥቂት አገራት ሁለት አኃዝ ተሻግሮ ከ25 እስከ 30 በመቶ ደርሷል" ሲሉ ተናግረዋል። ከሰሐራ በርሐ በታች የሚገኙ አገራት ከዓለም ገበያ የሚሸምቷቸው የምግብ ሸቀጦች እና የነዳጅ ዋጋ መጨመር ዋንኛ የዋጋ ንረት ገፊ ምክንያቶች መሆናቸውን ያስረዱት አበበ "አብዛኛዎቹ ቤተሰቦች ራሳቸውን ከዋጋ ንረት ሊታደጉ የሚችሉበት መላ እጅግ የተወሰነ በመሆኑ በቁጥጥር ሥር ሊውል ይገባል። ምክንያቱም የዋጋ ንረት ከተቀረው የማኅበረሰብ ክፍል ይልቅ በተለይ ተጋላጭ የሆኑት ላይ የሚበረታ ነው" ሲሉ ተደምጠዋል።

የአፍሪካ ማዕከላዊ ባንኮች የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር የሚወስዷቸው እርምጃዎች ግን በአገራቱ ኤኮኖሚ ላይ የሚያሳድሩት ተጽዕኖ መኖሩ አይቀርም። የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የአፍሪካ ክፍል ኃላፊ "የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር የሚወሰደው እርምጃ በዕድገት እና ለኤኮኖሚው በሚቀርብ ብድር ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር የሚችል ቢሆንም ከዚህ ቀደም በተለያዩ አገራት እንዳየንው ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት የበለጠ ጉዳት የሚያመጣ ነው" ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

ከ2021 ሁለተኛ መንፈቅ ወዲህ ከሰሐራ በርሐ በታች በሚገኙ የአፍሪካ አገራት ዓመታዊ የዋጋ ንረት 10 በመቶ ገደማ ነበር። የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት አዲሱ ትንበያ በተያዘው ዓመት 8.7% እንደሚሆን ከልሷል። የድርጅቱ ኃላፊ ክሪስታሊና ጂዮርጂየቫ በዋሽንግተን ባለፈው ሣምንት በተካሔደው የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት እና የዓለም ባንክ ዓመታዊ የጋራ ጉባኤ "በምግብ ዋስትና እጦት በተለይ በኃይል የተጎዱ 48 አገራትን ለይተናል። አብዛኞቹ ከሰሐራ በርሐ በታች የሚገኙ የአፍሪካ አገሮች በመሆናቸው እምብዛም አትገረሙም" ብለው ነበር። ብርቱ የምግብ ዋስት እጦት ይገጥማቸዋል ከተባሉት 48 አገራት እስከ 20 የሚሆኑት ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም እገዛ ይጠይቃሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ደብረ ማርቆስ ገበያ
በዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የአፍሪካ ክፍል ኃላፊ አበበ አዕምሮ ሥላሴ "አብዛኛዎቹ ቤተሰቦች ራሳቸውን ከዋጋ ንረት ሊታደጉ የሚችሉበት መላ እጅግ የተወሰነ በመሆኑ በቁጥጥር ሥር ሊውል ይገባል። ምክንያቱም የዋጋ ንረት ከተቀረው የማኅበረሰብ ክፍል ይልቅ በተለይ ተጋላጭ የሆኑት ላይ የሚበረታ ነው" ሲሉ ተደምጠዋል።ምስል DW/E. Bekele

የዕዳ ጫና በአፍሪካ የሚያስከትለው ዳፋ 

የአፍሪካ አገራትን በመጪው ዓመት የሚገዳደረው ሌላ ፈተና እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገራት ላይ የበረታው የዕዳ ጫና ነው። በመላው ዓለም የወለድ ምጣኔ ሲጨምር ከሰሐራ በርሐ በታች የሚገኙ የአፍሪካ አገራት በተለይ ከፍ ያለ ዕዳ ያለባቸው ለዓለም አቀፉ የካፒታል ገበያ ያላቸውን ዕድል ያጣሉ። ይኸ እንደ ጋና ያሉ አገራት ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት እገዛ እንዲጠይቁ እንዳስገደዳቸው አበበ አዕምሮ ሥላሴ አስረድተዋል።

በአይ.ኤም.ኤፍ የአፍሪካ ክፍልን የሚመሩት አበበ "ከወረርሽኙ በፊት በቀጠናው የዕዳ መጠን እየጨመረ ነበር። ለበርካታ አገራት ወረርሽኙ ይኸን ችግር የበለጠ አባብሶታል። ሌሎች ተጨማሪ ችግሮች የበለጠ ከባድ አድርገውት የዕዳ መጠን እየጨመረ መሔዱን ቀጥሏል" በማለት አሳሳቢነቱን ጠቁመዋል።

"የሁሉም አገሮች የዕዳ መጠን ዕድገት ቢያሳይም ሁኔታው አንድ አይነት አይደለም። ከሰሐራ በርሐ በታች ከሚገኙ 46 ገደማ አገራት መካከል ሰባት እና ስምንት የሚሆኑት የዕዳ ጫና ውስጥ ወድቀዋል" ያሉት አበበ አዕምሮ ሥላሴ  "ከፍተኛ የዕዳ ጫና ሥጋት" ጎራ የተመደቡ እንደሚገኙም ተናግረዋል።  ስለ መፍትሔው ሲናገሩ "በበርካታ አገሮች ተግባራዊ እየተደረጉ የሚገኙ የመካከለኛ ጊዜ ማሻሻያዎችን መቀጠል፣ የገቢ አሰባሰብ እና የወጪ ቁጠባን ማጠናከር የዕዳ ፈተናውን ሊቆጣጠሩት ይችላሉ። እነዚህ በቂ ሳይሆኑ ቀርተው አገሮች ከዕዳ አከፋፈል ማሻሻያ ተጠቃሚ ሊሆኑ የሚችሉባቸው አጋጣሚዎች አሉ። እንዲህ ሲሆን በአፋጣኝ የዕዳ አከፋፈል ማሻሻያ መጠየቅ እጅግ ጠቃሚ ነው" ብለዋል።

የተጓተተው የኢትዮጵያ የዕዳ አከፋፈል ሽግሽግ ድርድር 

ኢትዮጵያ፣ ቻድ እና ዛምቢያ ከሁለት ዓመታት በፊት የኮሮና ወረርሽኝ ያሳደረውን ተጽዕኖ ተከትሎ በተጀመረው የቡድን 20 የጋራ ማዕቀፍ (G20's Common Framework) በኩል የዕዳ አከፋፈል ማሻሻያ ለማድረግ ጥያቄ አቅርበው እስካሁን በመጠባበቅ ላይ የሚገኙ አገሮች ናቸው። ሶስቱ አገራት በዕዳ አከፋፈላቸው ላይ ለሚደረግ ሽግሽግ ቻይናን ጨምሮ ከአበዳሪዎቻቸው የሚያደጉት ድርድር ግን እጅጉን አዝጋሚ ሆኖ ይታያል።

የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ዳይሬክተር ክሪስታሊና ጂዮርጂየቫ  ሒደቱ እጅግ ዘገምተኛ መሆኑን አምነው "አሁን ግን በዓመቱ መጨረሻ የዛምቢያ እና የቻድ ይጠናቀቃል ብለን ተስፋ እናደርጋለን" ሲሉ በዋሽንግተን የዓለም ባንክ እና እርሳቸው የሚመሩት ተቋም ባካሔዱት ዓመታዊ የጋራ ጉባኤ ላይ አስረድተዋል።

ክሪስታሊና ጂዮርጂየቫ የዛምቢያ እና የቻድ ጥያቄ የመጨረሻውን መፍትሔ ሊያገኝ መቃረቡን ቢገልጹም ስለ ኢትዮጵያ ግን ያሉት ነገር የለም። ዶይቼ ቬለ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የኢትዮጵያ የዕዳ አከፋፈል ማሻሻያ ጥያቄ የደረሰበትን ደረጃ እና የገጠመውን እንቅፋት በተመለከተ ማብራሪያ ቢጠይቅም ዝርዝር ምላሽ ማግኘት አልቻለም። የድርጅቱ ቃል አቀባይ "በቡድን 20 የጋራ ማዕቀፍ በዕዳ አከፋፈል ማሻሻያ ጥያቄው ላይ ከኢትዮጵያ ጋር መሥራታችንን እንቀጥላለን" ሲሉ ለጥያቄው በኢ ሜይል መልሰዋል።

የኢትዮጵያ የገንዘብ ሚኒስትር ድኤታ እዮብ ተካልኝ
በዋሽንግተን ሲካሔድ በነበረው የዓለም ባንክ እና የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ዓመታዊ የጋራ ጉባኤ የተሳተፉት የኢትዮጵያ የገንዘብ ሚኒስትር ድኤታ እዮብ ተካልኝ ግን ሒደቱ አንድም በአገሪቱ እየተካሔደ በሚገኘው ጦርነት ሳቢያ እንደዘገየ ለሬውተርስ ተናግረዋል። ምስል DW/S. Muchie

በዋሽንግተን ሲካሔድ በነበረው የዓለም ባንክ እና የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ዓመታዊ የጋራ ጉባኤ የተሳተፉት የኢትዮጵያ የገንዘብ ሚኒስትር ድኤታ እዮብ ተካልኝ ግን ሒደቱ አንድም በአገሪቱ እየተካሔደ በሚገኘው ጦርነት ሳቢያ እንደዘገየ ለሬውተርስ ተናግረዋል። የሒደቱን መዘግየት "የሚያበሳጭ" ያሉት ዶክተር እዮብ እንቅፋት ለሆነው የአገሪቱ ጦርነት መፍትሔ ያበጃል ተብሎ የሚጠበቀው የሰላም ንግግር "በመጪዎቹ ጥቂት ሣምንታት ይጀመራል" የሚል ተስፋ አላቸው።

በፈረንሳይ እና በቻይናው ኤግዚም ባንክ ተባባሪ ሊቀ-መንበርነት የሚመራው የኢትዮጵያ አበዳሪዎች ኮሚቴ ባለፈው ነሐሴ የዕዳ ክፍያ እፎይታ ለኢትዮጵያ እንዲሰጥ ቢስማማም ጉዳዩ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ተጨማሪ ሥምምነት እንደሚሻ ሬውተርስ ዘግቧል።

ከዕዳ አከፋፈል ማሻሻያው በተጨማሪ ኢትዮጵያ አዲስ የተራዘመ የብድር አቅርቦት ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ብትጠይቅም ሒደቱ እጅጉን ተጓቷል። የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ቃል አቀባይ ለዶይቼ ቬለ በጉዳዩ ላይ በሰጡት ምላሽ "ሁኔታዎች ሲፈቅዱ" ለአዲስ የተራዘመ የብድር አቅርቦት ድርድር መንገድ ለመጥረግ በአገሪቱ የማሻሻያ ዕቅዶች እና የኤኮኖሚ ልማት ጉዳዮች ላይ በኢትዮጵያ ባለሥልጣናት እና በአይ.ኤም.ኤፍ ባለሙያዎች መካከል ውይይት እየተካሔደ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በመስከረም 2014 የተቋረጠው የተራዘመ የብድር አቅርቦት በአዲስ ሲተካ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ጠቀም ያለ ገንዘብ መጠየቋን ዶክተር እዮብ ተካልኝ ለሬውተርስ ቢናገሩም በትክክል መጠኑ ስንት እንደሆነ ግን ያሉት ነገር የለም። ዶክተር እዮብ የኢትዮጵያ መንግሥት "ግጭቱን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት በአቅሙ የቻለንውን ሁሉ እንዳደረገ የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ቦርድ ይረዳል" የሚል እምነት እንዳላቸው ለዜና ወኪሉ ተናግረዋል።

እሸቴ በቀለ

ኂሩት መለሰ