1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚኢትዮጵያ

የኤኮኖሚ ማሻሻያው “ቆንጠጥ የሚያደርግ ሆኖ ማስተካከል ይጠይቃል” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ

Eshete Bekele
ረቡዕ፣ የካቲት 6 2016

የኢትዮጵያ የኤኮኖሚ ማሻሻያ “ቆንጠጥ የሚያደርግ” ሆኖ ሊስተካከል እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እምነት አድሮባቸዋል። የዋጋ ግሽበት፣ ታክስ፣ የንግድ ሚዛን መጓደል ዐቢይ ከጠቀሷቸው ዋና ዋና ጉዳዮች መካከል ናቸው። “የኢትዮጵያ ሕዝብ በበቂ ደረጃ ታክስ እየተከፈለ እንዳልሆነ ተገንዝቦ ማሻሻያዎች ላይ ቢተባበር መልካም ነው” ብለዋል።

https://p.dw.com/p/4cOSQ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት
ዓለም ላይ በሚታየው ቀውስ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ በበረታው ግጭት፣ ጦርነት እንዲሁም በመንግሥት ላይ ላለፉት ዓመታት በነበረው “የማይነገር ጫና” ምክንያት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ “የማክሮ ኤኮኖሚ ስብራቶቻችንን በምናስበው ፍጥነት መጠገን አልቻልንም” ሲሉ ተናግረዋል።ምስል Fana Broadcasting Corporate S.C.

የኤኮኖሚ ማሻሻያው “ቆንጠጥ የሚያደርግ ሆኖ ማስተካከል ይጠይቃል” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የዋጋ ግሽበትን ጨምሮ የኢትዮጵያ ምጣኔ ሐብት የሚወዘውዙትን በርካታ ችግሮች ለመቅረፍ መንግሥት ተግባራዊ የሚያደርገው የኤኮኖሚ ማሻሻያ መርሐ-ግብር “እንደ ጥርስ ሐኪም ትንሽ ቆንጠጥ የሚያደርግ አድርገን ማስተካከል ይጠይቃል” ሲሉ ተደምጠዋል። ማሻሻያው “አሁን ላለው መንግሥት ላይጠቅመው ይችላል። ለትውልድ ግን በጣም ወሳኝ ነው” ያሉት ዐቢይ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በሰጡት ማብራሪያ “የምንቸገርባቸው ጉዳዮች በተወሰነ ደረጃ እልባት ሊያገኙ ይችላሉ የሚል ተስፋ አለ” ሲሉ ተናግረዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት የመጀመሪያውን ሀገር በቀል የኤኮኖሚ ማሻሻያ መርሐ-ግብር ተግባራዊ ማድረግ የጀመረው በ2012 ነው። በመርሐ-ግብሩ የኢትዮጵያን የውጭ ምንዛሪ እጥረት በዘላቂነት መፍታት እና በገበያ ፍላጎት የሚመራ ተለዋዋጭ የውጭ ምንዛሪ ግብይት ሥርዓት መዘርጋትን የመሰሉ ሥራዎች ታቅደው ነበር።

የመንግሥት የልማት ድርጅቶች የዕዳ ተጋላጭነት ለመቀነስ የአስተዳደር እና ቁጥጥር ሥርዓቱን ማጥበቅ፤ የአገር ውስጥ ገቢ አሰባሰብን ማጠናከር፤ የመንግሥት ወጪ ለድህነት ቅነሳ እና መሰረታዊ የመሠረተ-ልማት ግንባታ በሚያመች መንገድ ማቀላጠፍ ሁለተኛ ዓላማዎቹ ናቸው።

የኢትዮጵያን የፋይናንስ ዘርፍ እና አገሪቱ የምትከተለውን የገንዘብ ፖሊሲ የግል መዋዕለ-ንዋይን በሚያግዝ መንገድ ማሻሻል አራተኛ፤ የፋይናንስ አገልግሎት ደኅንነት ማዕቀፍን ቁጥጥር ማጠናከር ደግሞ አምስተኛ ሆነው ቢታቀዱም አልተጠናቀቁም።

ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ለሀገራት የሚሰጥ ብድርን የሚያመለክት ምስል
ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ሀገር በቀል የኤኮኖሚ ማሻሻያ መርሐ ግብር የመጀመሪያ ምዕራፍ 2.9 ቢሊዮን ዶላር ብድር ሰጥቶ የነበረ ቢሆንም ጦርነት ሲቀሰቀስ አቅርቦቱ ተቋርጧል። ምስል Maksym Yemelyanov/Zoonar/picture alliance

ዓለም ላይ በሚታየው ቀውስ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ በበረታው ግጭት፣ ጦርነት እንዲሁም በመንግሥት ላይ ላለፉት ዓመታት በነበረው “የማይነገር ጫና” ምክንያት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ “የማክሮ ኤኮኖሚ ስብራቶቻችንን በምናስበው ፍጥነት መጠገን አልቻልንም” ሲሉ ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መንግሥታቸው በሚከተለው የፊስካል ፖሊሲ “አሁን ብቻ ሳይሆን ለሚቀጥሉት መንግሥታትም ጭምር ፋይዳ ሊያመጡ የሚችሉ” ሥራዎች እንደተከናወኑ ያምናሉ። የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ያለባቸውን ዕዳ ለመቀነስ የተወሰደው እርምጃ እና ለነዳጅ ግብይት ይደረግ የነበረውን ድጎማ በሒደት ማቋረጥ “ከፍተኛ የሆነ እምርታ” ከታየባቸው መካከል ተብለው በምሳሌነት ቀርበዋል።

የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት “በዋጋ መዋዠቅ ምክንያት 180/190 ቢሊዮን ገደማ ዕዳ ነበረበት” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ይኸን በሒደት ለመፍታት በሠራንው ሥራ አሁን ወደ 100 ቢሊዮን ገደማ ዝቅ አድርገንዋል” ሲሉ ተደምጠዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ተግባዊ የሚያደርገው የኤኮኖሚ ማሻሻያ በገንዘብ ፖሊሲ ረገድ “ትልቅ ክፍተት” እንደገጠመው ጠቅላይ ሚኒስትሩ አምነዋል። የገንዘብ ተቀማጭ በ2015 ከነበረበት በ100 ቢሊዮን ብር ጨምሮ 1.2 ትሪሊዮን ብር መድረሱን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ይኸ የገንዘብ ዝውውሩን ስለሚቀንስ ግሽበት ላይ የሚያስገኘው ውጤት አለ” ሲሉ አስረድተዋል። በዐቢይ ማብራሪያ መሠረት ባንኮች ባለፉት ስድስት ወራት ካቀረቡት ከ170 ቢሊዮን ብር በላይ ብድር ውስጥ 83 በመቶው ለግል ዘርፍ የተሰጠ ነው።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የቀድሞ እና አዲስ ዋና መሥሪያ ቤት
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ “ንግድ ባንክ እና ልማት ባንክ ይወድቁ ነበር። ድነዋል፤ ችግር አላቸው፤ ሥራ ይፈልጋሉ ነገር ግን የነበረባቸው ወገብ አጉባጭ ስብራት በተወሰነ ደረጃ ተቃሏል” ሲሉ ተናግረዋል። ምስል Eshete Bekele/DW

“ንግድ ባንክ እና ልማት ባንክ ይወድቁ ነበር። ድነዋል፤ ችግር አላቸው፤ ሥራ ይፈልጋሉ ነገር ግን የነበረባቸው ወገብ አጉባጭ ስብራት በተወሰነ ደረጃ ተቃሏል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ  “በሞነተሪ እና ፊስካል ፖሊሲ ላይ የተወሰዱት እርምጃዎች ተሰናስለው ፤ አንደኛው አንደኛውን እየደገፈ የተሟላ ውጤት በሁሉም indicators ለማየት እንዳንችል ያደረገን አጠቃላይ ቀውሱ ነው” ሲሉ ተናግረዋል። ዐቢይ “ዕዳውን ወረስን፤ የምናደርጋቸው ለውጦች ደግሞ አዳዲስ ተግዳሮቶች ሲታከሉበት በተወሰነ ደረጃ በምናስበው ፍጥነት ልንፈታ አልቻልንም” ብለዋል።  

ዐቢይ በግብርናው ዘርፍ “ከፍተኛ እምርታ” መኖሩን፤ በኢንዱስትሪ “ኢትዮጵያ ታምርት” የሚባለው ንቅናቄ “ብዙ ለውጥ” ማምጣቱን ተናግረዋል። መንግሥታቸው ጀማሪ ኩባንያዎችን ለማበረታታት የሚያደርገው ጥረት እና በተያዘው ዓመት ሥራ ይጀምራል ተብሎ የሚጠበቀው የካፒታል ገበያ ለውጥ ያመጣሉ ብለው ተስፋ የሰነቁባቸው ናቸው።

የኢትዮጵያ ኤኮኖሚ በተያዘው ዓመት 7.9 በመቶ ገደማ ያድጋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተናግረዋል። የመንግሥታቸው ግምት የቀጠናው ሀገራት ይኖራቸዋል ተብሎ ከሚጠበቀው ምጣኔ ሐብታዊ ዕድገት እንደወትሮው ከፍ ያለ ነው። ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት በጎርጎሮሳዊው 2024 ከሰሐራ በርሐ በታች የሚገኙ ሀገራት ኤኮኖሚ በ3.8% ያድጋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ይፋ አድርጓል።

በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሪፖርት መሠረት የኢትዮጵያ መንግሥት በ2016 ስድስት ወራት ለማስገባት ካቀደው 270 ቢሊዮን ብር ውስጥ 265 ቢሊዮን ብር ሰብስቧል። ዐቢይ እንዳሉት ይኸ የገቢ መጠን ከ2015 አኳያ በ17 በመቶ ብልጫ አለው። የመንግሥት የገቢ መጠን ከኢትዮጵያ አጠቃላይ ሀገራዊ ምርት (GDP) አኳያ ከአስር በመቶ በታች መሆኑን የጠቀሱት ዐቢይ “በቂ ገቢ በማይሰበሰብበት ሀገር ውስጥ በቂ ልማት ማምጣት አይቻልም” ብለዋል።

ሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ
በ2016 የኢትዮጵያ ምጣኔ ሐብት በ7.9 በመቶ ያድጋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተናግረዋልምስል AFP/E. Jiregna

“ታክስ ላይ ማሻሻያ ያስፈልጋል” በሚለው ሐሳብ ሁሉም የጋራ አቋም መያዝ እንደሚገባው የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “የኢትዮጵያም ሕዝብ በበቂ ደረጃ ታክስ እየተከፈለ እንዳልሆነ ተገንዝቦ ማሻሻያዎች ላይ ቢተባበር መልካም ነው። ቶሎ ሰብስበን፤ አልምተን መውጣት ካልቻልን በስተቀር አይሆንም” የሚል ጥሪ አቅርበዋል።

ዐቢይ በምክር ቤቱ ስለ ኢትዮጵያ ምጣኔ ሐብት ይዞታ በሰጡት ማብራሪያ ሀገሪቱን ሰንጎ ስለያዛት የውጭ ምንዛሪ እጥረት እና የበጀት ጉድለት ምንም ያሉት ነገር የለም። የኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ እጥረት እንዲህ በቀላሉ የሚፈታ እንዳልሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዚህ ቀደም ተናግረዋል። የችግሩ ዋንኛ መነሾ የሆነው የገቢ እና ወጪ ንግድ ሚዛን መጓደል ዐቢይ “ርብርብ ይፈልጋል” የሚሉት ነው። 

በ2015 የመጀመሪያ ስድስት ወራት ሀገሪቱ ከወጪ ንግድ 10.5  ቢሊዮን ዶላር አግኝታ እንደነበር ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተያዘው ዓመት አምስት ወራት ውስጥ የተገኘው በአንጻሩ “ወደ 4.5 ቢሊዮን ዶላር” ብቻ መሆኑን ጠቁመዋል። “ከገቢ ንግድ አንጻር አምና ያስገባንው 17 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ነው። ዘንድሮ በአምስት ወር ውስጥ 7.5 ቢሊዮን ዶላር ኢምፖርት አስገብተናል” ሲሉ አስረድተዋል።

ባለፉት አምስት ወራት 1.5 ቢሊዮን ዶላር ቀጥተኛ የውጭ መዋዕለ ንዋይ ኢትዮጵያ እንዳገኘች ዐቢይ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት አስረድተዋል። ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሥራ ዕድል በተመሳሳይ ጊዜ ውስጥ መፈጠሩን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዚህ ውስጥ ከ150 ሺሕ በላይ የሚሆኑ ሰዎች ወደ ውጭ ሀገር መላካቸውን ጠቅሰዋል። 

የዐቢይን መንግሥት እና ኢትዮጵያውያንን በኃይል ለሚፈታተነው የዋጋ ግሽበት መፍትሔ ማበጀት ግን እንዲህ ቀላል አልሆነም። አቶ ማሞ ምኅረቱ የሚመሩት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የዋጋ ግሽበትን በመጪው ሰኔ መጨረሻ ከ20 በመቶ የማውረድ ዕቅድ አለው። የዋጋ ግሽበትን “ዝቅተኛ እና የተረጋጋ” አድርጎ ለመቆጣጠር ያቀደው ባንኩ በወለድ ተመን ላይ ወደተመሠረተ የገንዘብ ፖሊሲ ፊቱን አዙሯል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ማሞ ምኅረቱ
አቶ ማሞ ምኅረቱ የሚመሩት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የዋጋ ግሽበትን በ2016 ሰኔ መጨረሻ ከ20 በመቶ በታች የማውረድ ዕቅድ አለው።ምስል CC BY 2.0/U.S. Institute of Peace

“የንግድ ሰንሰለቱ ባለበት ችግር ምክንያት የዋጋ ንረትን በተሟላ ደረጃ፤ በምናስበው ልክ ልንፈታ አልቻልንም” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ግሽበቱ ከ35 በመቶ ወደ 28 በመቶ ዝቅ ማለቱን ጠቅሰው “መጠነኛ ውጤት” እንደታየ አስረድተዋል።

“በዋጋ ንረት ላይ እየወሰድን የነበረው የማሻሻያ [እርምጃ] በማስታገሻነት የሚታይ ነው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ቆንጠጥ የሚያደርግ እና በዘላቂነት የሚያክም ማሻሻያ መድፈር የሚፈልግበት ጊዜ እየደረስን መጥተናል” ሲሉ ወደፊት መንግሥታቸው ኮስተር ያለ እርምጃ ሊወስድ እንደሚችል ጥቆማ ሰጥተዋል።

የዋጋ ንረትን ለማረጋጋት የኢትዮጵያ መንግሥት የተከተለው የመጀመሪያ እርምጃ ስንዴ እና ሩዝ የመሳሰሉ የምግብ እህሎች ምርት ማሳደግ እንደሆነ ዐቢይ ተናግረዋል። በየዓመቱ እስከ 800 ሚሊዮን ዶላር ስንዴ ከዓለም አቀፍ ገበያ ለመሸመት መንግሥታቸው ወጪ ያደርግ እንደነበር የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “አሁን ለስንዴ አንድ ብር አናወጣም” ሲሉ ተደምጠዋል።

እሸቴ በቀለ