1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚኢትዮጵያ

ኢትዮጵያ በጦርነት የተመሰቃቀለውን መልሶ ለመገንባት ከባድ ሥራ ከፊቷ ተደቅኗል

Eshete Bekele
ረቡዕ፣ ጥቅምት 30 2015

በፕሪቶሪያ የተፈረመው "የግጭት ማቆም ሥምምነት" ተግባራዊ ሆኖ ጦርነት ካላገረሸ ኢትዮጵያ በውጊያ የወደመውን የመገንባት ብርቱ የቤት ሥራ ይጠብቃታል። የኢትዮጵያ መንግሥት የትምህርትና የጤና ተቋማትን ጨምሮ በጦርነቱ የወደመውን ለመመለስ 20 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልጋት ቢገምትም የኤኮኖሚ ባለሙያዎች ወጪው ከዚያ እጅጉን የላቀ እንደሚሆን ይጠብቃሉ

https://p.dw.com/p/4JHrG
በኢትዮጵያ ጦርነት የወደመ ታንክ
የኢትዮጵያ ፌድራል መንግሥት እና ህወሓት በደቡብ አፍሪካ ግጭት የማቆም ሥምምነት ከተፈራረሙ በኋላ ውጊያው ጋብ ብሏል። በሁለት ዓመታቱ ጦርነት የወደመውን መልሶ መገንባት ግን የአገሪቱን አቅም የሚፈታተን ነው። ምስል Tiksa Negeri /REUTERS

ከኤኮኖሚው ዓለም፦ ቢሊዮን ዶላሮች የሚሻው የኢትዮጵያ መልሶ ግንባታ ፈተና

ከሁለት ዓመት ደም አፋሳሽ ጦርነት በኋላ የኢትዮጵያ መንግሥት ፊቱን ወደ መልሶ ግንባታ ለማዞር እየተዘገጃጀ ነው። መቀመጫቸውን በአዲስ አበባ ላደረጉ የውጭ አገራት ዲፕሎማቶች እና የዓለም አቀፍ ተቋማት ኃላፊዎች የፌድራል መንግሥቱ እና ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ ስለ ተፈራረሙት ሥምምት ባለፈው ቅዳሜ ማብራሪያ የሰጡት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደሕንነት አማካሪ አቶ ሬድዋን ሑሴን የአገሪቱ አጋሮች ለመልሶ ግንባታው እንዲተባበሩ ጥሪ አቅርበዋል። አቶ ሬድዋን እንዳሉት ኢትዮጵያ ብርቱ ሰብዓዊ፣ ማኅበራዊ እና ኤኮኖሚያዊ ቀውስ ካስከተለው ጦርነት ለማገገም የሚያሻት ገንዘብ ግን እጅግ ከፍተኛ ነው።

ትምህርት ቤቶች፣ የጤና ተቋማት እና መንገዶችን ጨምሮ "የጠፋውን በሙሉ ለመመለስ 20 ቢሊዮን ዶላር ገደማ" እንደሚያስፈልግ የገለጹት አቶ ሬድዋን "የደረሰብን ከባድ ጉዳት ነው" ሲሉ ተደምጠዋል።

የፖሊሲ አውጪዎቹ ፈተናዎች

በዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡ ዘንድ የሚዘዋወረው ይኸ 20 ቢሊዮን ዶላር ግን መልሶ ግንባታ ላይ ብቻ ያተኮረ ነው። "የጠፋው የኤኮኖሚ አቅም" እና ኢትዮጵያ በጦርነቱ የደረሰባት ኪሳራ ግን ከተጠቀሰው 20 ቢሊዮን ዶላር እጅግ እንደሚልቅ በብሪታኒያው ኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ የኤኮኖሚ ባለሙያ የሆኑት እና የኢትዮጵያን ሁኔታ የሚከታተሉት ዶክተር ክርስቲያን ሜየር ይገምታሉ።

የኢትዮጵያ ፖሊሲ አውጪዎች "እጅግ ከባድ ተግዳሮት" እንደሚጠብቋቸው የገለጹት ዶክተር ክርስቲያን ሜየር "በመጥፎ ሁኔታ ላይ" የሚገኘውን የማክሮ ኤኮኖሚውን መረጋጋት መመለስ፤ እያንዣዣበበ ለሚገኘውን የዕዳ ቀውስ መፍትሔ ማበጀት እና በመልሶ ግንባታ እና ማገገም ላይ ኢንቨስት ማድረግ ቀዳሚዎቹ የቤት ሥራዎች እንደሆኑ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። ይሁንና የኤኮኖሚ ባለሙያው እንደሚሉት "ሶስቱንም በአንድ ላይ ማድረግ ቀርቶ አንዱን በተናጠል መከወን እጅግ ከባድ ነው የሚሆነው።"

የኢትዮጵያ ፌድራል መንግሥት እና የህወሓት ልዑካን ከአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪዎች ጋር
በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ ፌድራል መንግሥት እና ህወሓትን ወክለው ሥምምነት የተፈራረሙት አቶ ሬድዋን ሑሴን እና አቶ ጌታቸው ረዳ ናቸው። ምስል PHILL MAGAKOE/AFP

የኢትዮጵያ ፌድራል መንግሥት እና የህወሓት ሥምምነት የገጠመው ተቃውሞ

ኢትዮጵያ ፊቷን ወደ መልሶ ግንባታ ማዞር የምትችለው ግን በደቡብ አፍሪካዋ ፕሪቶሪያ የተፈረመው "የግጭት ማቆም ሥምምነት" ተግባራዊ ከሆነ እና ዳግም ግጭት ካላገረሸ ብቻ ነው። ሥምምነቱ ሁለት ዓመታት የዘለቀውን ደም አፋሳሽ ግጭት ያቆማል ተብሎ ተስፋ ቢጣልበትም በተለይ በውጭ አገራት ከሚኖሩ የትግራይ ብሔር ተወላጆች ዘንድ ብርቱ ተቃውሞ ገጥሞታል።

በኖርዌይ በርገን ዩኒቨርሲቲ የፒኤች ዲ ትምህርታቸውን የሚከታተሉት አቶ ሙሉ በየነ የፌድራል መንግሥቱ እና የህወሓት ሥምምነት "ወይ እጃችሁን ስጡ ወይም በረሐብ ሙቱ" የሚል አስገዳጅ ምርጫ መካከል የተፈረመ እንደሆነ ይተቻሉ። ሥምምነቱ "በነጻ ፈቃድ ሊሆን የማይችል" ሲሉ የሚገልጹት አቶ ሙሉ "ብዙ የሕግ ጥሰቶች የሚሸልም ስለሆነ በሕጋዊነቱ ላይ ጥያቄ ያስነሳል" ሲሉ ተናግረዋል።  ሥምምነቱ ከተፈረመ በኋላ "ፊት ለፊት የሚደረግ ጦርነት እንደነበረ ሰምተናል" የሚሉት የሕግ ባለሙያው "መሠረታዊ የሚባሉ አገልግሎቶችን መዝጋት፣ ማስራብ፣ ሌሎች የሚሰጡትን እገዛ እንዳይገባ ማድረግ ዋና የጦርነቱ ማካሔጃ መንገዶች ናቸው" ሲሉ ተናግረዋል።

ሁለት ዓመታት በዘለቀው ጦርነት የኢትዮጵያ መንግሥት "ምግብን እንደ ጦር መሳሪያ ተጠቅሟል" በሚል ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የቀረበበትን ክስ ሲያስተባብል ቆይቷል። በሰብዓዊ ዕርዳታ ሥርጭት ረገድ የቀረቡበትንም ወቀሳዎች አይቀበልም። መንግሥት የሰብዓዊ ርዳታዎችን በተቻለ አቅም ለማድረስ ጥረት ሲያደርግ እንደነበረም በተደጋጋሚ ይገልጻል። አቶ ሙሉ ለትግራይ ሕዝብ ሰብዓዊ ዕርዳታ እንዲቀርብ ማድረግ እና የተቋረጡ መሠረታዊ አገልሎቶችን ማስጀመር ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

የቴሌኮም ታወር በመቀሌ
በትግራይ የቴሌኮም እና የባንክን ጨምሮ መሠረታዊ አገልግሎቶች ተቋርጠዋል። የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት እና የመድሐኒት እጥረት እስካሁን መፍትሔ አልተበጀላቸውም። ምስል Million Hailessilassie/DW

እነዚህ ሥራዎች "ቀናነት ቢኖር ኖሮ በቀላሉ የሚደረጉ" እንደነበሩ የጠቀሱት አቶ ሙሉ "ጦርነት ስላለ ነው የቆመው የሚል" አመክንዮ አይዋጥላቸውም። "በእኔ አስተያየት የኢትዮጵያ ሥርዓት" የመልሶ ግንባታን ጉዳይ ያነሳው "የራሱን የገንዘብ እጥረት ለመድፈን" ነው የሚሉት አቶ ሙሉ "ትግራይን የሚመለከት ሊመጣ የሚችል ዕገዛ ቢኖር በራሱ ጊዜ የሚያስኬደው ነው የሚሆነው" ሲሉ ሥጋታቸው ለዶይቼ ቬለ አጋርተዋል። "የትግራይን ጥቅም ማስጠበቅ የሚችል ኃይል ተገዶ እጁን በሰጠበት ይኸ ነገር ቢኖር እንኳን ከጊዜ አንጻር ሌሎች ማድረግ የሚቻሉ ነገሮች ባልተደረጉበት ይኸ እምነት የሚጥል ነገር አይደለም" ሲሉ አስረድተዋል።

አቶ ሬድዋን ሑሴን ባለፈው ቅዳሜ በአዲስ አበባ በሰጡት ማብራሪያ ተቋርጠው የነበሩ የቴሌኮም እና የኤሌክትሪክ አገልግሎቶችን በአላማጣ በኩል ማገናኘት መጀመሩን አስረድተዋል። አቶ ሬድዋን እንዳሉት "በሌሎች አካባቢዎች በተለይም በምዕራብ በኩል" የጥገና ሥራ እየተከናወነ ይገኛል። የሰብዓዊ ዕርዳታን በተመለከተ መንግሥት መድሐኒት እና ምግብ ማሰራጨት መጀመሩን የገለጹት ሬድዋን "አጋሮች ለመግባት ዝግጁ መሆናቸውን ተረድተናል" ብለው ነበር። መቀመጫቸውን በአዲስ አበባ ላደረጉ ዲፕሎማቶች በሰጡት ማብራሪያ የኢትዮጵያ ወዳጆች እና አጋሮች ሥምምነቱን በበጎ እንደተቀበሉ የጠቀሱት አቶ ሬድዋን "በርካቶች የመልሶ ግንባታ ጥረቱን ለመደገፍ ፍላጎት አላቸው" ብለዋል።

"እንደምታውቁት በግጭቱ በኃይል የተጎዳው የትግራይ ክልል ነው። መንግሥት ክልሉን መልሶ ለመገንባት ያለውን ሐብት ለመመደብ ዝግጁ ነው። ፍላጎቱ ግን እጅግ ከፍተኛ ነው" ያሉት የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የብሔራዊ ደሕንነት አማካሪ የኢትዮጵያ አጋሮች እንዲያግዙ ጥሪ አቅርበዋል። የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ "ሁሉም አባላት ሥምምነቱን መደገፋቸው ጠቃሚ ነው" ያሉት አቶ ሬድዋን "ሁለተኛ ግምት አንቀበልም። ሁለቱ ወገኖች ተስማምተዋል። አገሪቱ ወደ ፊት መራመድ አለባት። ከአጋሮቻችን ጋር ያለንን ግንኙነትም ማደስ አለብን" ሲሉ ተደምጠዋል።

በጦርነት የተፈናቀሉ እናት ከልጆቻቸው ጋር
የዓለም ጤና ድርጅት ለትግራይ ክልል በአፋጣኝ የምግብ እና መድሐኒት ዕርዳታ እንዲቀርብ ጥሪ አድርጓል። በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መረጃ መሠረት ጦርነቱ ባመሳቀላቸው የትግራይ፣ አማራ እና አፋር ክልሎች ብቻ 9 ሚሊዮን የሚገመቱ ዜጎች እርዳታ ጠባቂ ሆነዋል። ምስል YASUYOSHI CHIBA/AFP

በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ የኤኮኖሚ ባለሙያው ዶክተር ክርስቲያን ሜየር በእርግጥም ኢትዮጵያ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አገዛ እንደሚያስፈልጋት ይስማማሉ። "ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ግዙፍ የኤኮኖሚ መልሶ ግንባታ ፓኬጅ በማዘጋጀት ሊያግዝ ይችላል" የሚሉት ክርስቲያን ሜየር "ማክሮ ኤኮኖሚውን ለማረጋጋት የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ፕሮግራም፤ በቡድን 20 ማዕቀፍ የዕዳ እፎይታ ለመስጠት የልብ ጥረት ማድረግ፤ ኤኮኖሚው እንዲያገግም ከዘርፈ-ብዙ (መልቲ ላተራል) እና የሁለትዮሽ (ባይላተራል) ለጋሾች ገንዘብ ማቅረብ እንዲሁም ኢትዮጵያ ወደ አፍሪካ የዕድገት እና ዕድል ድንጋጌ (አጎዋ) የምትመለስበትን ግልጽ መንገድ ማበጀትን ይጨምራል" ሲሉ አስረድተዋል።

"እንዲያም ሆኖ" ዶክተር ክርስቲያን ሜየር ለዶይቼ ቬለ እንዳሉት "ማክሮ ኤኮኖሚውን ማረጋጋት፣ የሚያንዣብበውን የዕዳ ቀውስ መግታት እና በመልሶ ግንባታ ላይ ኢንቨስት ማድረግ እጅጉን ከባድ ነው።"

የኢትዮጵያ ምጣኔ ሐብት በሚቀጥለው ዓመት በ5.3 በመቶ ያድጋል ብሎ የተነበየው ዓለም አቀፉ የገንዘብ "ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ለመመለስ ወሳኝ እርምጃ" ይወክላል ያለው ሥምምነት መፈረሙን በበጎ ከተቀበሉ አንዱ ነው።  "የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ሠራተኞች ከኢትዮጵያ ባለሥልጣናቱ ጋር በማሻሻያ መርሐ ግብራቸው ላይ ለአዲስ የብድር አቅርቦት ለመደራደር መሠረት ሊጥል የሚችል ውይይት እያደረጉ" መሆኑን የድርጅቱ ቃል አቀባይ በኢ-ሜይል ለዶይቼ ቬለ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ከድርጅቱ የጠየቀችው አዲስ የተራዘመ የብድር አቅርቦት መቼ እንደሚፈቀድቅም ይሁን አገሪቱ ከአበዳሪዎቿ ጋር የጀመረችው የዕዳ አከፋፈል ማሻሻያ መቼ እንደሚጠናቀቅ የገለጹት ነገር ባይኖርም የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ቃል አቀባይ  "ቀጣይ እርምጃዎችን ከግምት ውስጥ እናስገባለን፤ ከባለሥልጣናት ጋር በእነዚህ ጉዳዮች ላይ እንነጋገራለን" ብለዋል።

የአውሮፓ ኅብረት ቃል አቀባይ ናቢላ ማስራሊ"የሰብዓዊ ዕርዳታ በሁሉም ጦርነቱ በጎዳቸውና ባጎሳቆላቸው አካባቢዎች ማድረስ እና በትግራይ መሰረታዊ አገልግሎቶችን ማስጀመር" ቅድሚያ ሊሰጣቸው እንደሚገባ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። ይሁንና በጦርነቱ ምክንያት ሳይጸድቅ የቀረው የኅብረቱ አንድ ቢሊዮን ዩሮ የልማት ዕርዳታ እና የተቋረጠው የበጀት ድጋፍ ለኢትዮጵያ ይሰጥ እንደሁ ተጠይቀው መልስ ሳይሰጡ ቀርተዋል። የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ታኅሳስ 23 ቀን 2014 ያጣችውን የአፍሪካ የዕድገት እና ዕድል ድንጋጌ (አጎዋ) ተጠቃሚነቷን መልሶ ለማግኘት በቅድመ ሁኔታዎች ማሟላት እንደሚኖርባት አስረድተዋል።

እሸቴ በቀለ

ማንተጋፍቶት ስለሺ